የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ከክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመቀናጀት እያካሄደ የቆየው የመንገድ ደህንነት ቁጥጥር ሥራ ግብረመልስ ተገመገመ

የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ከክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመቀናጀት እያካሄደ የቆየው የመንገድ ደህንነት ቁጥጥር ሥራ ግብረመልስ ተገመገመ

የሲዳማ ክልል መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ከክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመቀናጀት በሀዋሳ ከተማና በአራቱም የክልሉ ዞኖች እያካሄደ የቆየውን የመንገድ ደህንነት ቁጥጥር ሥራ አፈጻጸም እና ግብረመልስ ገምግሟል።

በሁለት ቡድን ተከፍሎ የተሰማራው የቴክኒክ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል በሀዋሳ ከተማና በሁሉም ዞኖች በሚገኙ መናኸሪያዎችና ዋና ዋና የመንገድ አውታሮች ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳዩ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በሪፖርቶቹም የህግ ማስከበር እርምጃዎች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ የኢ-ቲኬቲንግ (E-Ticketing) አተገባበር እንዲሁም የ3ኛ ወገን መድን እና የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና አሰጣጥ ሂደቶች በዝርዝር ቀርበዋል።

በምልከታው ወቅት እንደ ችግር የተለዩ የ3ኛ ወገን መድንና የቴክኒክ ምርመራ (ቦሎ) አለማደስ፣ ሕገ-ወጥ ጊዜያዊ ወረቀቶችን መጠቀም፣ በሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ ማሽከርከር፣ ከመነሀሪያ ውጭ መጫን፣ ከስምሪት መስመር ውጭ መጓዝ፣ ከተፈቀደለት ውጪ መጫን እንዲሁም የመድን ፈንድ ክፍያ መዘግየት ጉዳዮች በትኩረት ተመላክቷል።

የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢ እና የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የመንገድ ደህንነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለማየሁ አሰፋ በግምገማው ወቅት እንደገለጹት፣ በመስክ ቁጥጥሩ የተለዩ ክፍተቶችን በማረም እና ችግሮቹ ዳግም እንዳይከሰቱ በማድረግ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል። አክለውም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የቴክኒክ ቡድኑ የሚያደርጋቸው ድንገተኛ ፍተሻዎችና የቁጥጥር ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

ይህንን ልጥፍ ያጋሩ

Comments are closed.